Translate

Saturday, January 5, 2013

በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች ከፍተኛ አለመረጋጋት እየታየ ነው፣ የሚይዝና ሚጨብጠውን ያጣው ዘረኛ የወያኔ አገዛዝ አስከፊ ርምጃ መውሰዱን ቀጥሏል


በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች ከፍተኛ አለመረጋጋት እየታየ ነው፣ የሚይዝና ሚጨብጠውን ያጣው ዘረኛ የወያኔ አገዛዝ አስከፊ ርምጃ መውሰዱን ቀጥሏል

በትናንትናው እለት ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ያካሄዱትን የጁምዓ ጸሎት ተከትሎ የዘረኛው ወያኔ አገዛዝ ወታደራዊ ሃይሎች አስከፊ ርምጃዎችን እየወሰዱ ሲሆን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን  ገዳዩ አገዛዝ እየተከተለ ያለውን አካሄድ በመተቸትና በመቃወም ላይ የሚገኙ መሆኑን ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ በላከልን ዘገባ ላይ አመለከተ።
እንደዘጋቢያችን ሪፖርት በሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች ሊባል በሚችል ደረጃ በሙስሊም ኤትዮጵያዊያን ላይ ያለው ክትትልና ጫና ከመቼውም ጊዜ በላይ የተባባሰ ሲሆን በተለይም፣ በሀረር ግጭቱ ከፍቶ አንድ ከ10 እስከ 12 ዓመት የሚገመት እድሜ ያለው  ወጣት መገደሉ ታውቋል። እንደዘጋቢያችን ሪፖርት ሃረር ውስጥ ሙስሊሞች በ4ኛ መስጊድ ተገኝተው  ስግደታቸውን ካደረሱ በሁዋላ በሰላም ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ባሉበት ወቅት የወያኔ  የፌደራል ፖሊስ አባላት የተወሰኑ ወጣቶችን ለማሰር በመፈለጋቸውና ከዚህም ጋር ተያይዞ ሙስሊሞቹ አላግባብ ወጣቶቹን ማሰር አትችሉም በማለታቸው ግጭቱ ሊነሳ ችሏል።

ህዝብ ለሚያቀርበው ሰላማዊና የመብት ጥያቄ ጥይትና ድብደባን ምልሽ በማድረግ የሚታወቁት የዘረኛው አገዛዝ ፖሊሶች በትናንትናው እለትም  በተኮሱት ጥይት ህጻኑን ከመግደላቸው በተጨማሪ እናቱንም እንዳቆሰሉዋት የአይን እማኞችን ዋቢ በማድረግ ዘጋቢያችን በላከልን ሪፖርት ገልጿል። በዚሁ በሃረር በተነሳው ግጭት ሌሎች ሶስት ነዋሪዎችም በጽኑ መቁሰላቸውንና በርካታ ወጣቶችም ታፍሰው ወደ እስር ቤት መወሰዳቸውን ዘጋቢያችን አክሎ ገልጿል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በወልድያ ደግሞ የጸጥታ ሀይሎች በርካታ ሙስሊም ወጣቶችን ይዘው ያሰሩ ሲሆን ወጣቶቹ የታሰሩት በአልበሲጥ መስጊድ ስግደት ካደረጉ በሁዋላና “መሀይም አይመራንም፣ የታሰሩ መሪዎቻችን ይፈቱ”፣ “መንግስት ሊመራ አልቻለም ይወረድ” የሚሉ መፈክሮችን በማሰማታቸው መሆኑን ዘጋቢያችን ወልዲያ የሚገኙ አንዳንድ ሙስሊሞችን በስልክ በማናገርና በማጠናቀር በላከው ዘገባ ገልጿል።
ህዝብን ርስ በርስ ማጋጨት እንደ ስልት አድርጎ የሚጠቀመው የወያኔ አገዛዝ ወልዲያ የሚገኙ በአነስተኛ እና ጥቃቅን የተደራጁ ወጣቶችን በማሰለፍ በሙስሊሞቹ ላይ  ጸረ ልማት የሚል ቅስቀሳ ለማካሄድ መሞከሩን፣  ያነጋገራቸው የወልዲያ ነዋሪዎች መናገራቸውን ዘጋቢያችን ገልጿል። በዚሁ በወልድያው ግጭት በርካታ ወጣቶች በፌደራል ፖሊስ መኪኖች እየተጫኑ ወደ እስር ቤት መወሰዳቸውን ተያይዞ የደረሰን ዘገባ አረጋግጧል።
በትናንትናው እለት ታላቁን የአንዋር መስጊድ ጨምሮ በደሴ፣ በአዋሳ፣ በሻሸመኔ እና በአዳማ ( ናዝሬት) ተመሳሳይ የተቃውሞ ድምጾች የተሰሙ ሲሆን ጨፍጫፊው የወያኔ አገዛዝ  የሙስሊሞችን ሰላማዊ ጥያቄ ከሽብርተኝነት ጋር እያያዘ ወደ አልሆ አቅጣጫ እየገፋው መምጣቱ ብዙዎችን ያሳሳበ ጉዳይ ሆኗል።
ይህ በንዲህ እንዳለ ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተው ግጭት ቀጥሎ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አሁንም በልዩ ጥበቃ ስር መሆኑን ዘጋቢያችን በላከልን ሪፖርት ገለጸ። እንደ ዘጋቢያችን ሪፖርት ከትናንት ማታ ጀምሮ የደህንነት ሀይሎች በኢህአዴግ ደጋፊ ተማሪዎች እየተመሩ ለግጭቱ መነሳት እና መባባስ ምክንያት ሆነዋል ያሉዋቸውን ተማሪዎች ስም ዝርዝር ማውጣታቸውና  የተወሰኑ ተማሪዎች በግዳጅ መታወቂያቸውን ተነጥቀው ወደ አልታወቀ ስፍራ መወሰዳቸው ታውቋል።
ወያኔ ሃያ አንድ አመት ሙሉ ሲቋጥር የከረመዉ የዘርና የጎሳ ችግር አዲስ አበባ የኒቨርሲቲ ዉስጥ ተማሪዎች ጎራ ለይተዉ እንዲደባደቡ ማድረጉን ዘጋቢዎቻቸን በላኩልን ዜና የገለጹ ሲሆን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲ ግቢ ዉስጥ በተፈጠረዉ የተማሪዎች ግጭት የኦሮሞና የትግራይ ተማሪዎች ጎራ ለይተዉ መደባደባቸውን፣ የግጭቱ  ስፋት ከዩኒቨርሲቲዉ ፖሊስ ቁጥጥር ዉጭ በመሆኑ አድማ በታኝና ግጭት አስወጋጅ የፌዴራል ፖሊሰ ወደ አካባቢዉ በፍጥነት መለኩን ዘጋቢዎቻችን አክለዉ ገልጸዋል። በዚህ ረቡዕ ምሸት ላይ ተጀምሮ ሐሙስ ጧት ላይ እንደገና ባገረሸበት ግጭት ብዙ ተማሪዎች ጉዳት ደርሶቸዉ ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱ ለማወቅ ተችሏል። ግጭቱን በወቅቱ ማብረድ የተሳነዉ የፌዴራል የፖሊስ ተማሪዎችን በካሚዮኖችና በፒክአፕ መኪናዎች እየጫነ ወዳልታወቀ ቦታ ወስዷል። ግጭቱ ወደ ስድስት ኪሎ ግቢ ተዛምቶ ከቁጥጥር ዉጭ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ያደረባቸዉ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ከአራት ኪሎ ወደ ስድስት ኪሎ የሚወስደዉን መንግድ ለሰአታት ዘግተዉት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። የፌዴራል ፖሊስ የግጭቱን መንስኤ ለመናገር ፈቃደኛ ባይሆንም ከአንዳንድ ተማሪዎች በተገኘዉ መረጃ መሠረት ግጭቱ የተፈጠረዉ በዩኒቨርስቲዉ የሚገኙ  የትግራይ ተማሪዎች የኦሮሚያን ተማሪዎች የሚያንቋሽሽ ንግግር አደርገዋል ጽሁፍም በትነዋል በሚል እንደሆነ ተናግረዋል።
በሌላም በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አለመረጋጋት በስፋት መቀጠሉና እጂግ አስጊ ሁኔታ ላይ እየደረሰ መሆኑ እየተገለጸ ሲሆ በደቡብ ክልል በቤንቺ ማጂ ዞን በቤሮ ሻሻ ወረዳ በሳሊ ቀበሌ በሚገኝ ባህላዊ የወርቅ ማዕድን ማውጫ መንደር በተከሰተው የእርስ በርስ ግጭት  ከ 162 ሰዎች በላይ መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት ዘግቧል።

    No comments:

    Post a Comment